የክብር ዶክትሬት ድግሪ የተሰጠው ጋሽ አበረ ምሕረቴ ማን ነው?


አንጋፋው የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የንስር ዓይኑን ተጠቅሞ በማኅበረሰባችን ውስጥ እጅግ ጉልህ አስተዋጽኦ ያደረገውን ጋሽ አበረ ምሕረቴን የክብር ዶክትሬት ድግሪ ሰጥቶታል። በደረሰብኝ የቤተሰብ ሀዘን ምክንያት ይህንን ትልቅ ዜና ሳላጋራ ብዘገይም ዛሬ በቻልኩበት ቀን ቢያንስ ጥቂት ነገር ማጋራት ይኖርብኛል። በአጠቃላይ አነጋገር ላለፉት ዐርባ ዓመታት የኢትዮጵያ ልሂቃን ለሀገራቸው ችግር የመፍትሄ አካል እንዳይሆኑ የሚያደርጉ በርካታ መዋቅራዊ መገለሎች የነበሩ ቢሆንም ከጥቂቶች በስተቀር አብዛኛው እንደ ጉዱ ካሳ ጉድለቶችን ብቻ እየነቀሱ ማውጣት ላይ እንጂ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ከፍሎ የመፍትሄው አካል የመሆን ጉዳይ አናሳ ነበር ማለት ይቻላል። ይህ ሁኔታ ነው ጋሽ አበረ ምሕረቴን በጣም ተለይቶ እንዲወጣ ያደረገው። ጋሽ አበረ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለመፍታትና የማኅበረሰብ ልማት ለማምጣት በተደረጉ ጥረቶች በመሪነትና በአስተባባሪነት መስራት የጀመረው አራት አስርት ዓመታት ቢሆነውም እጅግ ጉልህና አስገራሚ የነበረው ግን ከ20 ዓመታት በፊት በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በተለይም በጎጃም ውስጥ ተከስቶ የነበረውን አሰቃቂ የወባ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር የከፈለው መስዋዕትነት ነበር። ደጋማ በሚባሉት ወረዳዎች እንኳን ሳይቀር በሽታው በፍጥነት በመዛመት ቤተሰብና መንደርን ሙሉ እየጨረሰ አስከሬን የሚሸከም ሰው ጠፍቶ በአህያ እየተጫነ የሄደበትና በወጉ መቃብር ቆፍሮ መቅበር ያልተቻለበት ሁኔታ ፈጥሮ ነበር። ያን ያክል ሕዝብ እያለቀ የፐብሊክ ኸልዝ ኢመርጀንሲ ማወጅ፣ መድኃኒትና ባለሙያ ወደ ቦታው መላክ ይቅርና የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብና ዓለም ስለጉዳዩ እንኳን እንዲያውቀው ዜና አልተሰራም። ዛሬ ዓላማዬ ያ ለምን ሆነ የሚለውን መጻፍ አይደለም፤ ይልቁንም ጋሽ አበረ ያን ሁሉ አሸንፎ ገንዘቡን፣ ጊዜውንና ሕይወቱንም ጭምር መስዋዕት አድርጎ ሕዝቡን ስለመታደጉና ያንን ውለታውን ቢዘገይም የባሕር ዳር ዩኑቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ድግሪ ሰጥቶ ልቤን በደስታ ማረስረሱን ነው። ጋሽ አበረ የእርሱንና የጓደኞቹን ገንዘብ በማሰባሰብ በየገጠሩ በጓ ፈቃደኛ ሐኪሞችንና ነርሶችን ፋንሲደር ከተባለ የወባ መድኃኒት ጋር በማሰማራት እያደረገ የነበረው ጥረት ሽፋኑ እዚህ ግባ የሚባል ስላልነበረ የያኔውን ፀረ ወባ ማኅበርን ያሁኑ ጤና፣ ልማትና ፀረ ወባ ማኅበርን በማቋቋም እርዳታው የበለጠ ቅርጽ እንዲይዝ አደረገ። የዕርዳታ አሰባሰቡ፣ የባለሙያ ስምሪቱና አጠቃላይ የሕዝቡ ሞት ይገደኛል ማለቱ በወቅቱ መንግስት ነን ከሚሉ አካላት የሚጠይቀውን መስዋዕትነት አሁን ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም። ያም ሆኖ ያንን አሰቃቂ ወረርሽኝ ማቆም ከመቻሉም በላይ ያለፉትን 20 ዓመታት የድርጅቱን የትኩረት አቅጣጫ በማስፋት ለሀገሪቱ የጤና አጠባበቅ መርሐ ግብር ጉልህ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ቆይቷል። ወባን ከመከላከልና መቆጣጠር ባሻገር በኤች.አይ.ቪ መከለከልና መቆጣጠር፣ በወባና በኤድስ በሽታ ወልጆቻችውን ያጡ ህፃናትን በመንከባከብና ማሳደግ፣ በሥነ-ተዋልዶ ጤና፣ በማኅበራዊ ልማት፣ በአየር ንብረትና ጤና እንዲሁም በሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ የ.ተ.መ.ድ ተቋማት፣ የሀገሮች የልማት ተቋማትንና በአሜሪካ የሚገኙ ዕውቅ ዩኒቨርሲቲዎችን በማስተባበር፣ የሮተሪ ክበቦችንና የበጎ ፈቃድ ድርጅቶችን በየከተማው በማቋቋምና በመምራት ከፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የክልል ጤና ቢሮዎች ጋር በመተባበር እጅግ በርካታ ሥራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል። የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ለጋሽ አበረ ምሕረቴ የሰጠው የክብር ዶክትሬት ዲግሪ በኢትዮጵያ ውስጥ ለማኅበረሰብ ለውጥ አራማጆች ሁሉ የተሰጠ ክብር ነው ማለት ይቻላል። ምክንያቱም "ጋን በጠጠር ይደገፋል" ብለው የችግሩ ግዝፈትና መዋቅራዊ ማነቆው ሳይበግራቸው የአቅማቸውን ለማበርከት ደፋ ቀና በማለት ላይ ላሉና ከዚያም አልፈው እንደ ጋሽ አበረ ግዙፍ የማኅበረሰብ ችግሮችን ተዋግተው አሸንፈው አስተዋይ ያጡት ግለሰቦች ይህ የእርሱ ክብር የእነሱም ክብር ነውና። ከጋሽ አበረ የበጎ አድራጊነት ፍልስፍና የተቋደሳችሁትን ሁሉ እና ጋሽ አበረንም እንኳን ደስ አላችሁ እያልሁ ለዛሬ በዚህ አበቃለሁ። ወደ ፊት የጋሽ አበረን ስራዎች የሚዳስስ ሰፋ ያለ ጽሑፍ ለማጋራት እሞክራለሁ። እንኳን ደስ አለን! ሀምሌ 2010 ዓ.ም