HDAMA

የወባ ስርጭትን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት የሚደረገው ዘመቻ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጤና፣ ልማትና ፀረ ወባ ማህበር አስታወቀ፡፡

በአንከሻ ኮምንኬሽን

የወባ ስርጭትን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት የሚደረገው ዘመቻ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጤና፣ ልማትና ፀረ ወባ ማህበር አስታወቀ፡፡ግምጃ ቤት መጋቢት፡- 10/07/2013 ዓ/ም (አንከሻ ኮሙኒኬሽን) በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር በአንከሻ ጓጉሳ ወረዳ የወባ ስርጭትን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት የሚደረገው ዘመቻ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በአንከሻ ጓጉሳ ወረዳ የጤና ልማትና ፀረ-ወባ ማኅበር “የወባ ማህበራዊ ባህሪ ለውጥ ተግባቦት ፕሮጅክት” አስተባባሪ አስታወቁ ፡፡

በጤና፣ ልማትና ፀረ ወባ ማህበር የአንከሻ ጓጉሳ ወረዳ አስተባባሪ አቶ አጉማስ ሙላቴ እንደተናገሩት በወባማ ቀበሌዎች ማህበረሰቡ ስለወባ በሽታ ወረርሽኝ ያለውን አመለካከት፣ እውቀትና ግንዛቤ ለማሳደግ የማህበረሰብ ተኮር ግንዛቤ ትምህርት ተሰጥቷል፡፡ የማህበረሰቡ ግንዛቤ በመፈጠሩ ምክንያት ስርጭቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን የጠቀሱት አቶ አጉማስ ወባን በ2014 ዓ/ም ከወረዳ ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት አሁንም ትኩረት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ድንኩሻ ቀበሌ የበሽታ ስርጭቱ ከሚገኙባቸው ቀበሌዎች አንዱ ሲሆን ማህበረሰቡ በሚሰባሰብበት ገበያ ላይ ስለ ወባ በሽታ አስከፊነት የሚያስገነዝቡ መልዕክቶች በድራማ መልክ ተላልፈዋል፡፡ የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎችን መድፈንና ማፋሰስ፣ አጎበር ለታለመለት ዓላማ በአግባቡ መጠቀም እና በበሽታ የተያዘ ሰው ወደ ህክምና መውሰድ የሚሉ መከላከያ ዘዴዎችን ማህበረሰቡ በባለቤትነት ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

አቶ አልማው ወርቄ እና ወ/ሮ ጥሩ እንግዳ የዚህ ቀበሌ ነዋሪዎች ሲሆኑ በነበረን በተሳሳተ አመለካከት ምክንያት በወባ በሽታ በርካታ ሰዎች መጎዳታቸውን ተናግረዋል፡፡ ስለወባ ጎጂነት በባለሙያዎች በተሰጠው ግንዛቤ መሰረት ማህበረሰቡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ራሱን በመከላከሉ በሽታው እንዲቀንስ ተደርጓል ብለዋል፡፡ ተጎጂዎች እኛ በመሆናችን የግልና የአካባቢ ቁጥጥር ስራን በማጠናከርና አጎበርን በአግባቡ በመጠቀም ከወባ በሽታ ነፃ ማህበረሰብን ለመፍጠር ትኩረት ሰጥተው በጋራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡