ማኅበሩ በኮምቦልቻ ከተማ እየተገበረ ባለው የስነ-ተዋልዶ ጤናና ፆታዊ ጥቃት መከላከልና መቆጣጠር ፕሮጀክት ታላሚዎች ከሆኑት የኢንዱስትሪ ፓርክ ሰራተኞች እና ከማኅበሩ ሰራተኞች መካከል ለተመረጡ 20 ሰልጣኞች ከየካቲት 17 እስከ የካቲት 20 ቀን 2014 ዓ.ም ለ 4 ተከታታይ ቀናት በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የአቅም ግምባታ ማዕከል የአሰልጣኞች ስልጠና ሰጠ ፡፡
በስልጠናው ወቅት ሰልጣኞች በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ያገኙትን እውቀት ወደተግባር መተርጎም እንዲያስችላቸው የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ተግባራዊ ልምምድ በማድረግ ክህሎታቸውን አዳብረዋል ፡ ፡ በመቀጠል በኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች ላይ በጦርነቱ ምክንያት ለተከሰተው ቀውስ የስነ ልቦና መጀመሪያ ህክምና ርዳታ በመስጠት የማህበረሰቡን ስነ ልቦናና አዕምሯዊ ደህንነት ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ 240 የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ ስጭዎችን ከፕሮጀክቱ ታላሚዎች እና ከከተማው ኗሪዎች መካከል በመመልመል ለማሰልጠን ታቅዷል፡፡
ጤና ፣ልማትና ፀረ-ወባ ማኅበር በጦርነቱ ከቀያቸው ተፈናቅለው በኮምቦልቻና ደሴ ከተሞች ተጠልለው ለነበሩ ተፈናቃዮች ከ1.8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የብርድልብስና የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል፡፡