በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2019 ከተመዘገበው ሞት 43 በመቶ ያህሉ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ነው፡፡ በ2019 ለሞት ምክንያት ከሆኑት ከቀዳሚዎቹ አሥር ምክንያቶች ደግሞ ከልብ ጋር የተያያዙ በሽታዎች ከ55 በመቶ በላይ እንደነበሩ የዓለም ጤና ድርጅት የግሎባል ሔልዝ ዳሰሳ ያሳያል፡፡ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ዋና መንስዔ ከሚባሉ የሚመደብ ሲሆን፣ ይህም ከ2009 እስከ 2019 ባሉት ጊዜያት በ18 በመቶ ጨምሯል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን የደም ግፊት፣ ከልክ በላይ መወፈርና ኦብሲቲ በተከታታይ በ29.8 በመቶ እና በ81.4 በመቶ ጨምረዋል፡፡ በ2019 ከስትሮክ (ምት)፣ ከልብ ሕመምና ከጉበት ጋር የተያያዙ በሽታዎች ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ከተመዘገበው ሞት ከቀዳሚዎቹ አሥር ውስጥ ይመደባሉ፡፡ ከአመጋገብ ችግር ጋር በተያያዘ ከተመዘገበው ሞት ውስጥ ከአሥር ስምንት ያህሉ ከልብ ሕመም ጋር ሲሆን፣ 35 በመቶው ደግሞ ከደካማ የአመጋገብ ሥርዓት ጋር ተያይዘው በሚመጡ በሽታዎች የተከሰቱ ነበሩ፡፡ ይህንን ችግር የአመጋገብ ሥርዓት በማበጀት፣ ምግቦች ላይ ቁጥጥር በማድረግና ቁጥጥሩን በመተግበር መፍታት ያስፈልጋል የሚለው ጤና ልማትና ፀረ ወባ ማኅበር፣ ችግሩን ለመቅረፍ ከሚያስችሉ መንገዶች አንዱ በሆነው የምግብ ቁጥጥር ላይ እየሠራ ይገኛል፡፡ አቶ አክሊሉ ጌትነት የማኅበሩን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ምግብ ላይ ቁጥጥር መደረግ አለበት በሚል ማኅበሩ በጀመረው ፕሮጀክት ዙሪያ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡
-
-
-
Addis Ababa, Ethiopia