HDAMA

ወርቅነህ ጌታሁን

ከይልማና ዴንሳ ወረዳ - አባል

የጭንቅ ቀን ደራሽ

         በ1990ዎቹ መባቻ ድፍን ጎጃምን ከጫፍ ጫፍ በማዳረስ የሠውን ልጅ እንደቅጠል በማርገፍ እንደ ህውሃት ጁንታ ከፍተኛ የዘር ማጥፋት ያደረሰው የወባ ወረርሽኝ በተከሰተበት ስዓት የወገናቸው እልቂት የተሰማቸው ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ ከተማ የሆኑ 8 ቅን አሳቢወች ያቋቋሙት የያኔው ፀረወባ ማህበር ያሁኑ  ጤና፤ ልማትና ፀረወባ ማህበር ለተከታታይ ሁለት አስርት አመታት ወባና ኤች አይቪ ኤድስን በመከላከል ፤ በስነ ተዋልዶ ጤና እንዲሁም ወላጆቻቸውን በሞት የተነጠቁ ልጆችን ድጋፍ እና እንክብካቤ በማድረግ የሠራቸው ሥራዎች ሁሌም የሚታወሱና በወጣቱም ዘንድ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ምንነት እውቅና የፈጠረ ከመሆኑም በላይ በወባ ወረርሽኝ ሰዓት በቀን 9 እና 10 ሠው እየሞተ ቀባሪ በታጣበት ፤ አስከሬን የሚሸከም ታጦ ሬሳ በጋሬ በተጎተተበት ሰዓት ፤ የቤተሰብ አባላት በሙሉ አልቀው ቤት በተዘጋበት ሰዓት ፤ የወገኔ ህመም ህመሜ ነው ፤ የወገኔ ሞት ሞቴ ነው በማለት ከአንድ ቤተሰብ እማወራ በተነሳ ሀሳብ የተቋቋመው ይህ ማህበር ያከናወናቸውን በርካታ ሥራዎች በመዘርዘር ጊዜ ለማጥፋት ሳይሆን ፋና ወጊ በመሆን ያከናወናቸውን ጥቂት ሥራወች ለማስታወስ ያክል :-

  1. ማህበሩ በተቋቋመ ማግስት በጎጃም ክፍለ ሀገር (በምዕራብ ጎጃም ፤ በምስራቅ ጎጃም ፤ ባህርዳር ከተማ አስተዳደር እና በአዊ ዞን መተከልን ጨምሮ) በሚገኙ 29 ወረዳዎች የወረዳ ኮሚቴ በማቋቋም ወረዳዎችም  በየቀበሌው ኮሚቴና የአቻ ለአቻ አመቻቾችን በመምረጥ የወባ በሽታ ዋነኛ መከላከያ መንገድ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ በመሥራት የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎችን ማፋሰስ ፤ ማዳፈንና መጠቅጠቅ ሥራ እንዲሰራ ያደረገው  ትልቅ ዋጋ የሚያሰጠው ነው ፡፡ እኔም በምዕራብ ጎጃም ዞን የይልማና ዴንሳ ወረዳ ኮሚቴ በመሆን ወደ ማህበሩ የተቀላቀልኩት በዚሁ ወቅት ነበር ፡፡
      • ጤና ልማትና ፀረ ወባ ማህበር በ29 ወረዳወች የጀመረውን የወባ ቁጥጥር ሥራ አድማሱን በማስፋት ወደ ሰሜን እና ደቡብ ጎንደር በመግባት በ49 ወረዳወች ሰፊ ሥራ የሠራና በወባ ላይ የአቻ ለአቻ ውይይት በማድረግ ብቸኛ ማህበር ነው ፡፡
      • በ2ኛ ደረጃ እና በዩንቨርስቲ የሚማሩ ተማሪዎች በክረምት ትምህርት ቤት ሲዘጋ ከሦስት ቀን ያልበለጠ ስልጠና በመስጠት የአካባቢአቸውን ማህበረሰብ እንዲያስተምሩ በማድረግ ማህበረሰቡ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራን ባህሉ እንዲሆን ያደረገና የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ጠቀሜታ በወጣቱ ዘንድ ያሰረፀ ጤና፤ ልማትና ፀረወባ ማህበር ነው፡፡
      • ይህ የጤና፤ ልማትና ፀረ ወባ ማህበር የአቻ ለአቻ ሥራ ውጤታማነት ለጤና ኤክስቴንሽን መምጣት መነሻ ለመሆኑ ነቃሽ መቁጠር አያስፈልገውም ፡፡
  2. ማህበሩ በአቻ ለአቻ ዘማቾቹ አማካኝነት የአካባቢ ቁጥጥር ሥራን ከማጧጧፍ ጎን ለጎን በአዲስ አበባ የሚገኙ ቅን አሳቢ ወገኖቻችን በወባ ወረርሽኝ እያለቀ ስለሆነ በየድንኳኑ ለእዝን የምትሰጡትን አስቀድማችሁ እርዱን እና ቀድመን እንድረስላቸው በማለት አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከብር 500000.00 (አምስት መቶ ሺ ብር) በላይ በመሰብሰብ ፋልሲደር እና ኩኒን የወባ መድሃኒቶችን በመግዛት ይህን መድሃኒት ለመንግስት ብንሰጥ ለህሙማን የሚደርሰው   ከአመት በኋላ ነው ስለዚህ እራሳችን ይዘንላቸው ልንደርስ ይገባል በማለት አዲስ አበባ የሚገኙ  በጎ ፈቃደኛ የጤና ባለሙያዎችን በመያዝ የከፋ የወባ ወረርሽኝ ባለባቸው ወረዳዎች በመገኘት በሀኪም ተመርምረው የወባ በሽታ ላለባቸው ሰዎች ፊት ለፊት ውኃ እና መድሃኒት   በመስጠት በሞት አፋፍ ላይ የነበሩ ወገኖቻችንን ከሞት ተርፈው ፈጣሪአቸውን  እና ከሞት የታደጋቸውን ጤና ልማትና  ፀረ ወባ ማህበርን ዘወትር እየመረቁ የሚገኙ ወገኖች የዕድሜ ልክ ማስረጃዎች ናቸው፡፡
  3. ጤና ልማትና ፀረ ወባ ማህበር የወባ ወረርሽኝን በመከላከል ሥራ ላይ ሌት ተቀን ቢሰራም የሠዎች የሞት መጠን በታሰበው ልክ ሊቀንስ ባለመቻሉ ምክንያቱ ምንድነው ብሎ ሲአጠና የጥናቱ ውጤት ኤች አይቪ ኤድስ ያደከማቸውን ወባ ትገድላለች ስለዚህ በወባ  መከላከል ላይ ብቻ መስራት ብቻውን በቂ ስላልሆነ ከ1992 ዓ/ም ጀምሮ ኤች አይቪ አድስን በመከላከልና በመቆጣጠር ሥራ ላይ በመግባት የበሽታውን መተላለፊያና መከላከያ  መንገዶች በተለያዩ ያቻ ላቻ ውይይቶች ሰፊ ሥራ ከመስራቱም በላይ:-
      • በተለይም ኤች አይቪ ኤድስ ከናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ለማድረግ እናቶች በቤት ውስጥ እንዳይወልዱ የመንደር የልምድ አዋላጆችን በማሰባሰብ ግንዛቤ በመፍጠር በርግዝና ስዓት የሀኪም ክትትል እንዲአደርጉና ሲወልዱም ሀኪም ቤት መውለድ እንዳለባቸው ሪፈራል ካርድ በመጠቀም ከኢንትራ ሄልዝ ሀረግ ፕሮጀክት ጋር የሠራቸው ሥራወች መንግስት አሁን አንድም እናት በወሊድ አትሞትም አንድም ህፃን ከቫይረሱ ጋር አይወለደም ለሚለው መርህ መነሻው ይህ ጤና ልማትና ፀረ ወባ ማህበር የተጓዘበት ሂደት እንደሆነ ይታመናል ፡፡
  4. ለኤች አይቪ ኤድስ ግምባር ቀደም ተጋላጭ የሚሆኑ ወጣቶችን ቀድሞ ከጥቃት ለመታደግ ከ5ተኛ እስከ 8ተኛ ክፍል ለሚማሩ ልጆች (ተማሪዎች) በስነተዋልዶ ጤና ላይ የሠራው የአቻ ለአቻ ውይይት ሥራ ለማህበሩ ትልቅ ክብር ከሚአሰጡት ተግባራት አንዱ ነው፡፡
  5. ስለጤና ልማትና ፀረወባ ማህበር ሳነሳ ሁለት የማህበሩን ግንባር ቀደም ጀኔራሎች አለማንሳት መልክቴን ጎደሎ ስለሚአደርገው የሁለቱን ሄነሪዱናወች ተግባር ማንሳት የግድ ይለኛል
      1. ከላይ ሰለማህበሩ አመሰራረት ሳወሳ ከአንዲት እማወራ በተነሳ ሀሳብ ያልኩት እማወራዋ የማህበሩ መስራችና ዳሬክተር አቶ አበረ ምህረቴ ባለቤት ሲሆኑ አቶ አበረ ምህረቴ ማህበሩ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ከፍተኛ ሥራቸውን በመተው ሥራየ ከወገኔ አይበልጥብኝም በማለት ለሁለት አስርት አመታት ዳሬክተር በመሆን ማህበሩ ለሠራቸው ሥራዎች ሁሉ ዋነኛ ተዋናኝ ከመሆናቸውም በላይ በማህበሩ እየተደገፈች ዩንቨርስቲ የምትማር ተማሪ ለማስመረቅ በሚሄዱበት ሰዓት በተፈጠረ የመኪና አዳጋ እስከሞት ደርሰው የነበረ የማህበሩ የጀርባ አጥንት በመሆናቸው  ስለሳቸው ትንሽ ማውሳት የግድ ይለኛል ፡፡
      2. ማህበሩ ከተመሰረተ ጀምሮ ለቅስቀሳና የአቻ ለአቻ ማወያያ የሚሆኑ ጥቂት ስለኤች አይቪ ኤድስ ፤ የወባ በሽታ መተላለፊያና መከላከያ መንገዶቹ ፤ ዕድሮች ለልማትና የመሳሰሉትን በመፃፍና የአማራ ክልል ጤና ልማትና ፀረወባ ማህበር አስተባባሪ በመሆን ሰፊ ሥራ የሠሩትን ዶ/ር መኮንን አይችሉህምን ማስታወስ የማህበሩን ሥራዎች ማስታወስ ነው ፡፡
  6. ይህ የወገን ደራሽ የሆነ ማህበር በሽታዎችን ከመቆጣጠር ጎን ለጎን ወላጆቻቸውን በሞት የተነጠቁ ልጆችን በመደገፍና በመንከባከብ እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ያስመረቀ ስመ ጥር ማህበር ሲሆን አብዛኛዎቹ የማህበሩ ልጆች ማህበሩ በባህር ዳር ከተማ ባቋቋመው ጤና ጣቢያ ተቀጥረው በማገልገል ላይ ይገኛሉ ፡፡

              በጥቅሉ ጤና ልማትና ፀረ ወባ ማህበር ያከናወናቸውን ሥራዎች በሙሉ መዘርዘር ታዳሚን ማሰልቸት በመሆኑ ሀሳቤን በዚህ ልቋጭ እና ማህበሩ ባሁኑ ስዓት:-

      1. ማህበሩ ወባና ኤች አይቪ ኤድስን በመከላከልና በመሳሰሉ ጤና ነክ ተግባራት ሲአከናውን የነበረው እንቅስቃሴ ደረጃ በደረጃ እየቀነሰ ስለመጣ ወደ ቀድሞ ግለቱ እንዲመለስ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ
      2. ኮቪድ 19 ዓለምን ባንቀጠቀጠበትና ለሀገራችንም ከፍተኛ ስጋት በነበረበት ሰዓት ጤና ልማትና ፀረ ወባ ማህበር ካለው የግንዛቤ ፈጠራና የመፈፀም አቅም አንፃር ፈጥኖ እንደሚገባ ተስፋ ያደረኩ ቢሆንም ካለበት የፋይናንስ አቅም ውስንነት የተነሳ ፈትኖ የኮሮና ቫይረስን መከላከል ስራ ላይ ለመግባት ባለመቻሉ ማህበሩን በፈፃሚነት በመጠቀም በኮቪድ መከላከል ሥራ ላይ እንዲሠራ የሚመለከተው አካል ሁሉ እንዲደግፈው ጥሪየን በማስተላለፍ ሀሳቤን እቋጫለሁ ፡፡