logo

Apr 30 2025

የሲቪክ ማህበራት ጥምረትን በመወከል ክቡር ዶ/ር አበረ ምሕረቴ ሚያዚያ 18 2017 ዓ.ም በጅማ ከተማ በተከበረው 18ኛወ የዓለም የወባ ቀን አከባበር ባደረጉት ንግግር የጥናትና ምርምር ስራዎች ለተሻለ የጤና አጠባበቅ ስርዓት ያለውን ፋይዳ ገልፀው፣ አዳዲስ ፈጠራዎችንና ሀብትን በማቀናጀት በሁሉ አቀፍ ቁርጠኝነት ወባን ለመግታት ለህብረተሰባችን ድምፅ እንሆናለን ብለዋል።

‘የተከበራችሁ የሃይማኖት መሪዎች፣የተከበሩ የጤና ሚንስትር ዲኤታ ዶ/ር ደረጀ ድጉማ፣ የተከበሩ የኢ/ት በሸታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር ዳይሬክቶሬት ዶ/ር ህይወት ሰለሞን፣ የተከበሩ አቶ ጠሃ ቀመር የጅማ ከተማ ከንቲባ፣ የተከበሩ ፐሮፌሰር ነጻነት ወርቅነህ የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ሃላፊ፣ የተከበራችሁ የሲቪክ ማሀበራት ሃላፊዎችና ተውካዮች፣ የተከበራችሁ የመንግስት ባለስልጣናትና ተወካዮች፣ የተከበራችሁ የጅማ ከተማ ነዋሪዎች እና ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች. . . የዛሬ የተሰበሰብነው ሌላ የዓለም የወባ ቀንን ለማክበር ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱ ከዚህ በሽታ ሸክም ነፃ ለመሆን ያለንን ቁርጠኝነት ለማረጋገጥ ነው። ወባ ህይወትን እየቀጠፈ፣ ማህበረሰባችንን እያዳከመ እና እድገታችንን እየገታ ያለ ከባድ ፈተና ሆኖ ቀጥሏል። ከመንግስት አካላት፣አለም አቀፍ ለጋሾች እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ጎን እንደ የሲቪል ማህበረሰብ ደርጅቶች ተወካይ እዚህ መቆሜ በአንድ ላይ ለአንድ ዓላማ መቆም ዘላቂ ለውጥ እንደሚያመጣ ማስረጃ ነው።

ዛሬ፣ የዓለም የወባ ቀንን ምክንያት አድርገን በተሰበሰብንበት ወቅት፣ በጋራ ወባን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ያደረግናቸው አስደናቂ እመርታዎች እንዲሁም ከፊታችን ስላሉ ፈተናዎች እናሰላስላለን። ወባ በሃገራችን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን እያጠቃ፣ የሚወዷቸውን ቤተሰቦች እየነጠቀ፣ የኢኮኖሚ እድገትን እያደናቀፈ እና የጤና አጠባበቅ ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ያለ ትልቅ የህብረተሰብ ጤና ስጋት ነው። እንዴት መከላከል እንደሚቻል፣እንዴት እንደምናክመው እና አንድ ቀን ሙሉ በሙሉ ከሃገራችን እንዴት ጨርሶ ማስወገድ እንደሚቻል የምናውቀው በሽታ ነው።

ወባ የጤና ጉዳይ ብቻ አይደለም፣ የኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ብሎም የእድገት ጸር ነው። በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች፣ በጣም ተጋላጭ የሆኑትን የማህበረሰብ ክፍሎች ያለርህራሄ የሚያሰቃይ ነፍሰጡር እናት፣ ጨቅላ ህጻናት፣ ለህመምና ሞት የሚዳርግ ተማሪ ከትምህርቱ፣ ገበሬው ከእርሻ ፣ቤተሰባቸውን ለመደገፍ በልማት ቀጠናዎች በጊዚያዊነት ተንቀሳቅሰው የሚሰሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከስራቸው ሲስተጓጎሉና ሲስቃዩ አይተናል ። ወባን በመከላከል ረገድ ሁልጊዜም ረፍት እንዳይኖረንና ወደ ኋላ እንዳንል የሚያደርገን ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች እለት እለት የሚያጋጥመው የወባ ጫና ታሪክ ነው።

በዚህ የአለም የወባ ቀን፣ የአጋርነት ጥሪያችንን በድጋሚ እናስተላልፋለን። መንግስት ለጠንካራ ፖሊሲዎች፣ ለምርምር ስራዎች፣ ለመከላከል ፣ለምርመራና ህክምና ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በቅንጅት ወባን ለማስወገድ ቅድሚያ እንዲሰጥ እናሳስባለን። ለጋሾች፣ ድርጅቶች እና ግለሰቦች በየአካባቢያቸው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን። ምክንያቱም ለወባ መከላከል የሚውለው እያንዳንዱ ገንዘብ ህይወትን ስለሚታደግ መንግስት ሃብትን በማቀናጀት ወባን ለማስወገድ ቅድሚያ እንዲሰጥ እናሳስባለን። በመንግስት፣ በለጋሾች፣ በየግል ድርጅቶች እና በግለሰቦች

ለተደረጉት ጥረቶች፣ ሳይንሳዊ ግኝቶች፣ የተሻሻሉ የመከላከያ ስልቶች እና ጠንካራ የጤና አጠባበቅ ስርዓቶች እውቅና እንሰጣለን። ዛሬ ግን እራሳችንን እና አጋሮቻችንን የበለጠ እንድንሰራ እንሞግታለን።ሰው ተኮር መፍትሄዎች ላይ ፈሰስ ማድረግ፣የጤና አጠባበቅ መሠረተ ልማትን ማጠናከር፣ ሁለንተናዊ የነፍስ አድን የምርመራና ሕክምና መሳሪያዎችን ተደራሽነት ማረጋገጥ የርብርቡ ግንባር ቀደም ሆነው መቀጠል አለባቸው።

ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የማህበረሰቡ ድምጽ ናቸው። እንደ ጤና ልማትና ጸረ-ወባ ማህበር የወባ በሽታ ጫና የመጀመሪያዎቹ ምስክሮች እኛ ነን። ልጆች ማደግ ሳይችሉ፣ ቤተሰቦች በህክምና ወጪ ሲታገሉ እና በርካታ ህይወት በአጭር ሲቀጭ ተመልክተናል። በአንጻሩ ደግሞ የማህበረሰቡን ጫናውን የመቋቋም አቅምንም አስተውለናል። ቤተሰቦች ልጆቻቸው በፀረ-ትንኝ ኬሚካል በተነከረ አጎበር ውስጥ እንዲተኙ ሲያደርጉ፣ ወጣቶች ማህበረሰብ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የአካባቢ ቁጥጥር ዘመቻ ሲያደርጉ፣ የጤና ባለሙያዎች የሰው ህይወት ሲታደጉ አይተናል። ለበርካታ ዓመታት ከማህበረሰቡ ጋር በቅርበት በመስራታችን ቁርጠኝነቱን፣አይበገሬነቱን እና እምቅ አቅሙን የመፈተን እድሉን አግኝተናል። ለዚያም ነው ለማህበረሰብ ተሳትፎ ቅድሚያ የሚሰጡ ፖሊሲዎች እንዲወጡ የምንገፋፋው፣ ይህም በጣም ተጋላጭ ለሆኑ በተለይም በልማት ቀጠናዎች በጊዚያዊነት ተንቀሳቅሰው ለሚሰሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የወባ መከላከል እና ሕክምና አገልግሎቶችን በቀጥታ ለማድረስ የመፍትሄ ሃሳቦችን በመቅረጽ ላይ ተደራሸነት እንዲኖራቸው ለማድረግ መንግስትን እያገዝን ያለነው።

ዛሬም ጥሪያችን ግልፅ ነው፡ የመንግስት አካላት፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ለጋሾች እና ግለሰቦች የዓለም ጤና ድርጅት በ 2030 ወባን ለመቀነስና ለማስወገድ ያስቀመጠውን ግብ ለመድረስ የሚያስችሉንን የፈጠራ ስራዎች እንደግፍ። እያንዳንዱ ቤተሰብ የትም ይኑር የት፣ ምቹ የሆነ አኗኗር ይኑረውም አይኑረውም፣ ገቢው ከፍተኛም ይሁን ዝቅተኛ ወባን በብቃት ለመዋጋት የሚያስችል መሳሪያ እንዳለው እናረጋግጥ።

አመሰግናለሁ”

See insights and ads

Boost post

Like

Comment

Share

admin

Leave A Comment

Our Maps

© 2024 Copyright by Merciitsolution