logo

Jan 02 2026

በልማት ኮሪደሮች ለሚሰሩ ተንቀሳቃሽ ሰራተኞች የሚሆን አገራዊ የወባ መከላከልና መቆጣጠር መመሪያ ረቂቅ ላይ ውይይት ተካሄደ – አዲስ አበባ

የጤና ልማትና ፀረ-ወባ ማህበር (HDAMA) ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር፣ በልማት ኮሪደሮች ለሚሰሩ ወቅታዊ ተንቀሳቃሽ ሰራተኞች (Seasonal Mobile Workers) የሚሆን አገራዊ የወባ መከላከልና መቆጣጠር የአፈጻጸም መመሪያ ረቂቅ ላይ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የውይይት መድረክ አካሄደ።

ከታህሳስ 21 እስከ 22 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደው በዚህ የምክክር መድረክ ላይ፣ በሰፋፊ የእርሻ ቀጠናዎች፣ በማዕድን ስፍራዎች እና በግንባታ ስራዎች ላይ በጊዜያዊነት ተሰማርተው ለሚሰሩ ወገኖች የሚሰጠውን የወባ መከላከልና ቁጥጥር ስራ በስርዓት ለመምራት የሚያስችል ሰነድ ላይ ጥልቅ ውይይት ተደርጓል።
ይህ አዲስ መመሪያ በዋናነት ተንቀሳቃሽ ሰራተኞች ባሉባቸው የልማት ቀጠናዎች ውስጥ ለሚከናወኑ የወባ መከላከል ስራዎች አጠቃላይ መመሪያን ለመስጠት የታለመ ሲሆን፤የሚከተሉትን ዝርዝር ዓላማዎች አንግቧል፡-

  • ለባለድርሻ አካላት ውጤታማ አፈጻጸም እንዲኖር ግልጽ የአተገባበር መመሪያዎችን መስጠት፤
  • በዘርፉ በተሰማሩ ሁሉም ባለድርሻ አካላት መካከል ያለውን ትብብርና ቅንጅት ማሳደግ፤
  • የወባ መከላከልና መቆጣጠር እርምጃዎች ዘላቂነት እንዲኖራቸው ማድረግ፤
  • በልማት ኮሪደሮች የጤና ስራን የሚያጠናክሩ ፖሊሲዎች እንዲወጡ በፖሊሲ አውጪዎች ዘንድ የቅስቀሳ (Advocacy) ስራዎችን መስራት።

የጤና ልማትና ፀረ-ወባ ማህበር ከፈረንሳይ መንግስት (Expertise France) በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በአማራ ክልል በሚገኙ አምስት ወረዳዎች የእርሻና የልማት ቀጠናዎች ለሚሰሩ ጊዜያዊ ሰራተኞች የወባ መከላከልና ህክምና አገልግሎቶችን በቀጥታ ለማድረስ የሚያስችል ፕሮጀክት እየተገበረ ይገኛል። አሁን ለውይይት የቀረበው አገራዊ መመሪያም በዚህ ፕሮጀክት ድጋፍና ክትትል ሲዘጋጅ መቆየቱ ተገልጿል።

በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካዮች፣ የሚመለከታቸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ ዓለም አቀፍ ለጋሾች፣ የኢምባሲዎች እና የአጋር ድርጅቶች ተወካዮች የተገኙ ሲሆን፤ረቂቅ መመሪያው በልማት ኮሪደሮች የሚታየውን የወባ በሽታ ጫና ለመቀነስ እና የሰራተኞችን ጤና ለመጠበቅ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው መግባባት ላይ ተደርሷል።

admin

Leave A Comment

Our Maps

© 2024 Copyright by Merciitsolution